- አንዳንድ የሙናፊቅ ምልክቶች መገለጻቸው እርሱ ላይ ከመውደቅ ለማስፈራራትና ለማስጠንቀቅ ነው።
- ከሐዲሡ የተፈለገው ቁምነገር እነዚህ ነገሮች የንፍቅና ጉዳዮች እንደሆኑ፣ ባለቤቱ በነዚህ ጉዳዮች ከመናፍቃን ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ፣ የነርሱን ባህሪ የተላበሰ እንደሆነ ማሳወቅ ተፈልጎ ነው እንጂ እስልምናን ግልፅ እያደረገ ክህደትን የሚደብቅ ሙናፊቅ ሆኗል ለማለት ተፈልጎበት አይደለም። እነዚህ ነገሮች ያመዘኑበት፣ በነርሱ የተሳነፈና ያቃለላቸው አብዛኛው ሰው እምነቱም ብልሹ የሆነ ነው በሚልም ተተርጉሟል።
- ጘዛሊ እንዲህ ብለዋል: «የሃይማኖት መሰረት በሶስት ነገሮች ላይ የታጠረ ነው:- ንግግር፣ ተግባርና ኒያ ናቸው። በውሸታምነት ንግግራቸው ብልሹ እንደሆነ፣ አደራ በመካድ ድርጊታቸው ብልሹ እንደሆነ፣ ቃልን በማፍረስ ኒያቸው ብልሹ እንደሆነ አስገነዘበ። ምክንያቱም ቃልን ማፍረስ የገባውን ቃል ተቃርኖ የመተው ቁርጠኝነት እስከሌለው ድረስ የሚያስነውር ተግባር አይባልም። ቃሉን ለማክበር ቁርጠኛ ሆኖ ከዚያም እንዳያከብር የሚያደርገው ከልካይ ነገር ወይም ቃሉን ለመለወጥ የተሻለ ሀሳብ ቢያጋጥመው ይህ የሙናፊቅ መለዮ አልተገኘበትም ነው የሚባለው።
- ንፍቅና ሁለት አይነት ነው: እምነታዊ ንፍቅና: ይህ ሰውዬውን ከኢማን የሚያስወጣው ነው። ይህም እስልምናን ግልፅ አድርጎ ክህደትን መደበቅ ነው። ሌላው ተግባራዊ ንፍቅና: እርሱም ከመናፍቃን ጋር በባህሪያቸው መመሳሰል ነው። ይህም ሰውዬውን ከኢማን አያስወጣም። ነገር ግን ከትላልቅ ወንጀሎች መካከል አንዱ ነው።
- ኢብኑ ሐጀር እንዲህ ብለዋል: «ዑለማዎች ባጠቃላይ በቀልቡም በምላሱም አምኖ ነገር ግን እነዚህን ነገሮች የሰራ ሰው በክህደት እንደማይፈረጅና በእሳት የሚዘወትር ሙናፊቅ እንደማይሆን ተስማምተዋል።»
- ነወዊ እንዲህ ብለዋል: «የተወሰኑ ዑለሞች እንዲህ ብለዋል: እዚህ ሐዲሥ ውስጥ የተፈለጉት መናፍቃን በነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ዘመን የነበሩ በውሸት አምነናል ብለው የተናገሩ፣ በእምነታቸው ታምነው የካዱ፣ በሃይማኖት ጉዳይ እስልምናን ሊረዱ ቃልገብተው ቃላቸውን ያፈረሱ፣ በሙግቶቻቸው ጥመትን ይዘው የተሟገቱ ናቸው።»