- ኢማሙ ነወዊይ እንዲህ ብለዋል፦ ይህ በሸሪዓ ውስጥ ቀጣይነት ያለው መርህ ነው። እርሱም ልብስና ሱሪ መልበስ፣ ጫማ መልበስ፣ መስጂድ መግባት፣ ጥርስን መፋቅ፣ መኳል፣ ጥፍርን መቁረጥ፣ ቀድሞ ቀመስን ማሳጠር፣ ፀጉር ማበጠር፣ የብብት ፀጉርን መንጨት፣ ጭንቅላትን መላጨት፣ ከሶላት ማሰላመት፣ የንፅህና አካላትን መታጠብ፣ ከሽንት ቤት መውጣት፣ መብላት፣ መጠጣት፣ መጨባበጥ፣ ጥቁሩን ድንጋይ ሰላም ማለትና የመሳሰሉትን በዚሁ ደረጃ ላይ ያሉ ክብርና ልቅና ያለውን ነገር በቀኝ መጀመር ይወደዳል። በተቃራኒው የሆነ ነገር ደግሞ ሽንት ቤት መግባት፣ ከመስጂድ መውጣት፣ መናፈጥ፣ ኢስቲንጃእ፣ ልብስና ሱሪ ማውለቅ፣ ጫማ ማውለቅና የመሳሰሉትን በግራ መጀመር ይወደዳል። ይህ ሁሉም ቀኝ ክብርና ልቅና ስላላት ነው።
- "ቀኝን መጠቀም ይወዱ ነበር።" የሚለው: ድርጊቶችን በቀኝ እጅ፣ በቀኝ እግር ፣ በቀኝ ጎን፣ መጀመርንና ነገሮችን በቀኝ መቀባበልን ያካትታል።
- ነወዊይ እንዲህ ብለዋል: «ከዉዱእ አካላት መካከል ቀኝን ማስቀደም የማይወደድበት አካላቶች አሉ። እነርሱም ሁለቱ ጆሮዎች፣ ሁለቱ መዳፎችና ጉንጮች ሲሆኑ እነዚህ ሁሉ እኩል ነው የሚፀዱት። ይህንን ማድረግ የማይችል አካሉ የተቆረጠና መሰል (አንድ ላይ ማድረግ የማይችል) አይነት ከሆነ ቀኝን ያስቀድማል።»